CEO’s Interview with National Construction Magazine

ልጅ ሄኖክ፡- ከአንባብያን ጋር ለመተዋወቅ ይረዳን ዘንድ ስለትምህርት ዝግጅትህና ተያያዥ ጉዳዮች ጠቆም አድርገን፤

ልጅ ሄኖክ፡- ከአንባብያን ጋር ለመተዋወቅ ይረዳን ዘንድ ስለትምህርት ዝግጅትህና ተያያዥ ጉዳዮች ጠቆም አድርገን፤

   PRECISE ኮንሰልት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሄኖክ አሰፋ

PRECISE የቢዝነስ እና ኢኮኖሚ ልማት አማካሪ ድርጅት፣ ከመንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ኢንተርናሽናል ድርጅቶች ማለትም እንደ ዓለም ባንክ እና USAID ጋር የሠራን ሲሆን፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ለሚመጡ የውጭ እና የአገር ወስጥ ባለሀብቶች ስለኢንቨስትመንት የማማከር አገልግሎት ስንሰጥ፣ በተለይ ዓለማቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች የግል ክፍለ ኢኮኖሚውን እንዴት ማሣደግና ሞተር መሆን ይችላሉ በሚለው ጉዳይ ላይ አብዛኛውን ጊዜ ሠርተናል፡፡ የመንግሥት ድርጅቶችም ቢሆኑ አሠሪ የሆኑ ፖሊሲዎችን በማውጣት የግል ክፍለ ኢኮኖሚውን እንዴት ሊደግፉና ዘለቄታዊ በሆነ መንገድ ማሣደግ ይችላሉ በሚለው ጉዳይ ላይ ላለፉት አሥራ አንድ ዓመታት የማማከር አገልግሎት በመስጠት ቆይተናል ማለት ነው፡፡

ናሽ.ኮን፡- እንደሚያውቁት የሀገራችን ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዕድገት ካስመዘገቡ የሀገሪቱ ክፍለ ኢኮኖሚዎች ቀዳሚው ነው፤ የእርስዎ ዕይታ ምን ይመስላል?

አቶ ሄኖክ፡- ስለኮንስትራክሽን ዕድገት ቀን በቀን በምናደርገው ንግግር ውስጥ ብዙም ላይገባን ይችላል፡፡ ሆኖም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላለፉት አሥር እና አሥራ ሁለት ዓመታት በሁለት አኀዝ እያደገ መጥቷል ስንል፣ በተለይ ከተመዘገበው ውስጥ ዕድገቱ የመጣው ከየትኛው ዘርፍ ነው ስንል /Growth accounting/ በምንለው ቀመር፣ ኮንስትራክሽን ላይ ያለው ግብኣት ከሁሉም በልጦ መገኘቱን ነው፡፡

እንግዲህ ኮንስትራክሽን ስንል በውስጡ በርካታ ዘርፍ ይዟል፡፡ ከዚህ ውስጥ የግል አልሚው ሲገኝ የህዳሴው ዓይነት ግድብም በዚህ ውስጥ ተካታች ነው፡፡ ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለችው የመንገድ ዝርጋታና ማስፋፊያ ፕሮጀክት ከሌሎች አፍሪካ አገራት የላቀ እንደሆነ አስባለሁ፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙ ዜጎች የሥራ ዕድልና ልምድ ማግኘት እንደቻሉ ሲታወቅ ጥቂት ኢንጅነሮችና አርክቴክቶች ጎረቤት ሀገራት ሄደው መሥራት እየቻሉ ነው፡፡ የህዳሴውን ግድብ ጨምሮ በሌሎች የሀገሪቱ ግንባታዎች ላይ እየሣተፉ የሚገኙ ባለሙያዎች ወደፊት መላውን አፍሪካ የሚወሩ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም እዚህ አገር የተገነባው አቅም በሌሎች አፍሪካ አገራት የለም፡፡

ናሽ.ኮን፡- ግልጽ ቢደርጉልን?

አቶ ሄኖክ፡- ለምሳሌ የህዳሴው ግድብ በዓለም ካሉ ታላላቅ ግድቦች ውስጥ የሚመደብ ሲሆን ግንባታው እየተከናወነ የሚገኝበት ቴክኖሎጂያዊ አቅም ሌሎች አፍሪካ አገራት ውስጥ እስካሁን አልታየም፡፡ በዚህ ግድብ ሥራ ውስጥ ከአምስት ሺህ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን እየተሳተፉ መሆናቸው ሲታወቅ፣ በዚህ ግንባታ እያካበቱት ያለው የሥራ ልምድ በቀላሉ መታየት የለበትም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በታላላቅ የመስኖ፣ የመንገድ፣ የሕንፃ እና የባቡር መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ እየሠሩ የሚገኙ ዜጎች፣ እየገበዩ የሚገኘው የቴክኖሎጂ አቅም ሲታሰብ ኢትዮጵያውያን የኮንስትክራሽን ባለሙያዎች በውጩ ገበያ የሚኖራቸውን ተወዳዳሪነት ያሳያል፡፡

በመሠረቱ ደግሞ እነኮርያ እነቻይና ያደጉበት መንገድ ይኸው ነው፡፡ በሀገራቸው የተገበሩትን ነው ኢትዮጵያም መጥተው እየሠሩ የሚገኙት፡፡ በአጭሩ ለመግለጽ ኮንስትክራሽን በኢትዮጵያ ለኢኮኖሚ ልማቱ እያደረገው ያለው አስተዋጽዖ በደንብ ያልተዘመረለት መስሎ ይታየኛል፡፡ እርግጥ ቱሪዝም ትልቁ የሥራ ዕድል ፈጣሪ ቢሆንም፣ ኮንስትራክሽንም የርሱን ያህል ለአያሌ ዜጎች መጋቢ መሆን ችሏል፡፡ ሰሞኑን እንኳ በተፈጠረው አንዳንድ ሁኔታ ሥራው ቀዝቀዝ በማለቱ የተከሰተውን ክፍተት መታዝብ ችለናል፡፡

ናሽ.ኮን፡- የሀገሪቱ የኮንስትራክሽን ዘርፍ በአብዛኛው መንግሥታዊ ሲሆን የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ድርሻ በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ ነው፡፡ ዕድገቱ የአንድ ወገን አይመስልዎትም?

አቶ ሄኖክ፡- እርግጥ ኢንቨስትመንቱ በሰፊው የተያዘው በመንግሥት በኩል ነው፡፡ ሥራው የሚሠራው ግን አሁንም ቢሆን በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ነው፡፡ መንግሥት የግሉ ዘርፍ መሥራት ይችላል በሚለው ፕሮጀክቶች ሁሉ ጨረታ ያወጣል፡፡ እርግጥ በተወሰኑ ሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ የውጮቹ ካምፓኒዎች ተጋፍተው እየገቡ መሆናቸውን እናውቃለን፡፡ ይህ በአንድ በኩል ጥሩ ነው፤ ምክንያቱም ቴክኖሎጂያዊ ሽግግርን ሊያመጣ ይችላልና ነው፡፡ ከዚህ ውጭ መንግሥት በኮንስትራክሽን ውስጥ ያለው ድርሻ ያን ያህል ትልቅ ነው ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ መንግሥት በኢኮኖሚ ውስጥ ትልቁን በጀት ለመሠረተ ልማት በማዋሉ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚም ተጠቃሚ ሆኗል ባይ ነኝ፡፡

ናሽ.ኮን፡– የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ተጠቃሚ ሆኗል ከተባለማ በተለይ የውጮቹ ካምፓኒዎች ናቸው የሚሉ አሉ፡፡ ሀገር በቀሉ በውጮቹ ተወረርኩ እያለ እኮ ነው…?

አቶ ሄኖክ፡- በዚህ ጉዳይ ላይ ጠንከር ያለ አስተያየት ለመስጠት ቁጥሮችን አላየሁም፡፡ እርግጥ የውጮቹ ካምፓኒዎች እየገቡ ነው፡፡ በሌላ በኩል የመንግሥትን አካሄድ ከተመለከትከው፣ በፖሊሲና በአሠራር እንደተቀመጠው የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ይበረታታሉ፡፡ እንዲያም ሆኖ አንዳንድ ፕሮጀክቶች ላይ ለውጮቹ ቅድሚያ እየተሰጠ ነው የሚል ቅሬታ መሰማቱ አልቀረም፡፡ ግን በአብዛኛው ከተመለከትከው እኔም አንዳንድ አገራትን ማየት እንደቻልኩት፣ በጥራትና በተሻለ ዐቅም ለሚሠራ የውጭ ኮንትራክተር ሥራ የመስጠት ነገር አለ፡፡ በእኛ ሀገር ግን  በተቃራኒው ልምድ ለማካበትና ለማበረታታት ሲባል፣ ለሀገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ፕሮጀክቶች ቢሰጡም መጓተትና የጥራት ጉድለት አስከትለዋል የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ ያም ሆኖ መንግሥት ሀገር በቀል ኮንትራክተሮችን ለማብቃትና የኮንስትራክሽን ግብኣት አቅራቢዎችን ዐቅም ለማሳደግ በማኅበራትና በልዩ ልዩ አደረጃጀት ይህን ያህል መጓዙን እንረዳለን፡፡

ናሽ.ኮን፡- ሀገር በቀል ኮንትራክተሮች ከመንገድና ከሕንፃ ሥራ ተቋራጭነት በቀር በመስኖ  እና የማዕድን ዘርፍ መሰማራት አለመቻላቸው ይታያል ይህ ለምን ይመስልዎታል?

አቶ ሄኖክ፡-  የአቅም ጉዳይ ካልሆነ በቀር የሙያዊ  ብቃት ችግር ቀስ በቀስ እየተቀረፈ የመጣ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ በግንባታው ዘርፍ ላለፉት አሥርና አሥራ ሁለት ዓመታት የተገኘው የሥራ ልምድ ስትመለከተው በሕንፃ ዲዛይንና ግንባታ ጥሩ ጥሩ ነገር መመልከት ችለናል፡፡ እርግጥ የተወሰነ ጉድለት ቢኖርም ማለት ነው፡፡

እንደምታወቀው ኮንስትራክሽን ማለት በተፈጥሮው ከፍተኛ መዋዕለ  ነዋይ የሚፈስበት ነው፡፡ የውጮቹ የበለጡን በዚህ እንጂ አንድ ሀገር በቀል ኮንትራክተር የውጭ ማኔጀር አስመጥቶ መቅጠር ይችላል፡፡  በርግጥ የተወሰኑ ኮንስትራክሽን ካምፓኒዎች ይህን ማድረግ ችለዋል፡፡ ሌሎችም ወደዚህ ይመጣሉ የሚል ተስፋ ይኖራል፡፡

በዚህ ረገድ መንግሥት ምን ማድረግ ይችል ነበረ ወደሚለው ጥያቄ ስንመጣ፣ የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ በፋይናንስ ማጠናከር እንዳለበት ነው፡፡ በርግጥ ዘርፉን ለማሻሻል የተደረገ ጥናት ቢኖርም መንግሥት የያዛቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች የውጭ ምንዛሪውን እየወሰዱ ነው፡፡ ይሄ ማለት የገንዘብ ፍሰቱ ወደ አንድ ወገን ያጋደለ ነው፣ እንደ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በአንድ በኩል ኮንስትራክሽን ሴክተሩን እንደ ማነቆ ሊይዘው የሚችለው ይህ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

ናሽ.ኮን፡- እንደ ማነቆ ሲሉኝ ኮንስትራክሽን ሴክተሩ ከፍተኛ ሙስና ከሚታይበት አንዱ ነው መባሉንስ እንዴት ያዩታል?

አቶ ሄኖክ፡- በዓለማቀፍ ደረጃም ቢሆን ኮንስትራክሽን ሴክተር ለሙስና የተመቻቸ መሆኑን እንመለከታለን፡፡ ስለዚህ በእኛ አገር አዲስ አይመስለኝም፤ ምናልባት ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብዙ ብልሹ ነገሮች መፈጠራቸው ያሳስባል፡፡ ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ የበለፀጉ ሰዎች መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ ፍትሓዊ ያልሆኑ ውድድሮችና ጨረታዎች በግሉም በመንግሥትም ውስጥ ተባብረው የሚያጠፉት ጥፋት አለ፡፡ መንግሥት በዚህ ላይ ትኩረት ቢሰጥ ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ዘርፉ በየጊዜው ከማደጉ ጋር ተጣምሞ ካደገ የሕዝብ ሀብት ሊባክን ይችላልና ነው፡፡ ግን ሌቦቹ ሁለቱም ቦታ ነው ያሉት፡፡

ናሽ.ኮን፡- በኮንስትራክሽን  ማማከር ውስጥ ብዙ ሙያተኞች በየድርጅቶቻቸው ይገኛሉ፡፡  ግን በዋጋ ሰበራ እና በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው አማካሪዎችን የማግለል ነገር እንዳለ ይሰማል፡፡ ይሄን  እንዴት ያዩታል?

አቶ ሄኖክ፡- በዘርፉ ጠለቅ ያለ ዕውቀት ባይኖረኝም፣ በመርህ ደረጃ ውድድር መጥላት የለብንም፤ ያልተገባ ውድድር ብሎ ነገር የለም፡፡  ሕጉ እስካልተጣሰ ድረስ ለኔ ውድድር ጥሩ ነገር ነው፡፡ አንደኛ ገዢውን ማመን መቻል አለብን፡፡ ዋጋ ሰበራ ሲባል እኮ ገዢው አያውቅም እንደ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በዘርፉ ልምድ ያካበቱ አማካሪዎች ዋጋ ሰብረው የሚወዳደሯቸው ሌሎች አማካሪዎች ሲመጡባቸው የተሻለ ተወዳዳሪ መሆን ይጠበቅባቸዋል እንጂ ከነርሱ በታች ያሉትን ከተቀናቀኑ ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውም ጥሩ አይደለም፡፡

እርግጥ አጭበርባሪዎች ካሉ አንደኛ በሕግ፣ ሁለተኛ ደግሞ በተግባር ስለሚለዩ ዘርፉን ጥለው መውጣታቸው አይቀርም፡፡ ስለዚህ ገበያው ቢወስን ወይም ለገበያው ቢተው ይሻላል፡፡ በሌላ በኩል ሴክተሩ የሚዘምንበትን መመሪያዎችንና ደንቦችን ማወጣት ችግሩን ያቀለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግሥት ብቻ ሳይሆን የግሉ ኮንስትራክሽን በባለቤትነት መምራት ይገባዋል፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማኅበር አለ፡፡ አባላቱ ገበያውን በመምራትና ግንዛቤ በመስጠት መሥራት ይችላሉ፡፡ በሌሎች አገራት የግሉ ዘርፍ ነው የመሪነት ሚና የሚጫወተው፡፡

ናሽ.ኮን፡- ጥራትን እንዴት ማምጣት ይቻላል?

አቶ ሄኖክ፡-  የሚሻማና የሚወዳደር የግል ዘርፍ ሲፈጠር ጥራትም አብሮ ይመጣል፡፡ አሁን ለምሳሌ የግል ባንኮችን መመልከት እንችላለን፡፡ እርስ በርስ የሚያደርጉት ውድድር እየጨመረ ነው፡፡ ማናጀሮች ይደውላሉ፤ ከዛሬ አምስትና ስድስት ዓመት በፊት ግን እንኳን ሊደውሉ ይቅርና የራሳችንን ብር ለማወጣት እንኳ እንዴት እንቸገር እንደነበር ትዝ ይለናል፡፡ ስለዚህ ኮንስትራክሽን አማካሪዎች በዚህ ደረጃ መወዳደር ይኖርባቸዋል ባይ ነኝ፡፡ አሁን በኛ ዘርፍ እንኳ ኮፒ ፔስት እያደርጉ የሚወዳደሩ አማካሪዎች በርካታ ናቸው፤ ግን ይዘጋባቸው ብዬ አላወቅም ምክንያቱም እነርሱ ተደራሽ የሆኑበት ገበያ አለ፡፡ እኔ ግን ከእነርሱ ተሽዬ መገኘት አለብኝ፡፡

ናሽ.ኮን፡- ደንበኞች ወይም አሠሪዎች ርካሽ ገንዘብ ማግኘታቸውን እንጂ ግንባታቸው የሚገጥመውን ጥራት አይረዱም፤ ስለዚህ አሠሪዎችን እንዴት ማስገንዘብ ይቻላል?

አቶ ሄኖክ፡- ዋጋ ሰባሪዎች ሕገወጥ ሥራ ነው እየሠሩ ያሉት የሚለው አያሳምነኝም፡፡ ነገር ግን በገዢና ሻጭ መሀል ላለው ድርድር እኔ አውቅላችኋለሁ ማለት በጣም ይከብዳል፡፡ ምክንያቱም የሚያውቁትን ያህል ያውቃሉ፡፡ የማማከር አገልግሎት ሰጪው ትክክለኛ አገልግሎት ካልሰጠ ድጋሚ ወደርሱ የሚሄድ አይኖርም፡፡

ናሽ.ኮን፡- እንደሚያውቁት መንግሥት በቤት ልማት ላይ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው፡፡ የግል አልሚዎችም የውጮቹን ጨምሮ በሪል እስቴት ግንባታ የራሳቸውን ተሳትፎ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ገበያውና ፍላጎቱ እንዴት እየሄደ ይመስልዎታል?

አቶ ሄኖክ፡- በቂ አይደለም፡፡ እንደሚታወቀው ይህ ሴክተር በጣም ክፉ ጊዜዎችን አሳልፏል፡፡ ብዙ ሊባሉ የሚችሉ የሪል እስቴት አልሚዎች፣ ቃላቸውን ባለመጠበቃቸው ሳቢያ የገበያውን ተአማኒነት ለረዥም ጊዜ አናግተውት ቆይተዋል፡፡ ግን በርግጠኛነት የምነግርህ ገበያው ላይ  የቤት ፍላጎቱ ከፍተኛ መሆኑን ነው፤ የመንግሥትንም ጨምሮ ማለት ነው፡፡ የዚህ መነሻ ደግሞ ከዛሬ ስድስትና ሰባት ዓመታት በፊት የኮንስትራክሽን ዕድገት በሰፊው ተስፋፋ እንጂ  ከአርባና ሠላሳ ዓመታት በፊት በሀገሪቱ ምንም ዓይነት ኮንስትራክሽን አልነበረም ማለት ያስችላል፡፡ ይህ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲንከባለል የመጣው ፍላጎት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊሟላ አላስቻለም፡፡

በዚህ ላይ ደግሞ ኢኮኖሚው እያደገ ነው፤ የሰው አቅም ቀስ በቀስ እየጨመረ ነው፤ ባንኮችም ጠንካራ ፖሊሲ ተጭኗቸውም ቢሆን እያደጉ በመጡ ቁጥር እነርሱም ፋይናንስ ማድረግ እየጀመሩ ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ፍላጎቱን ጨምሯል፡፡ በመንግሥትም በኩልም ሰፊ ዕቅድ ተይዞበትና የሥራ ዕድል ለመፍጠርና ሀገር በቀል ኮንትራክተር ለመፍጠር ታሳቢ ተደርጎ ጊዜ እየፈጀ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የኮንደሚኒየም ግንባታው በታሰበው ፍጥነት አለመሄዱ ታይቷል፡፡ ይህም የቤት ፍላጎቱን አንሮታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ እያደገ ያለው አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን መላው ሀገሪቱ ነው፡፡ ክፍለ ሀገር አቅሙ ያደገው ቤት መግዛት የሚፈልገው በአዲስ አበባ ነው፡፡ ስለዚህ በጥቂት ብር ከሚገዙ ቤቶች ጀምሮ እስከ ሚሊየኖች ብር ድረስ የቤት ገበያው እንዳለ ነው የሚገባኝ፡፡ አሁን ሠርቶ የሚያቀርበው አካል አለመገኘትና በአንድ ወቅት በዚህ ዘርፍ የተከሰተው የደንበኞች አመኔታ ማጣትን የሚሞላ ባለሀብት መምጣት ነው፡፡ በርግጥ መጥተዋል፣ ግን እንደሚታሰበው አይደለም፡፡

ናሽ.ኮን፡- እንዲያስ ቢባል ሪል እስቴቶች የቤት ፈላጊውን ሕዝብ ጥያቄ ይመልሳሉ ተብለው ተስፋ ይደረጋሉ?

አቶ ሄኖክ፡- እውነት ለመናገር ከባድ ነው፡፡ ምክንቱያም አሁን በአገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ ሌሎች ተግዳሮቶች ስላሉና እነብረት፣ እነአሉሚኒየም ዋጋ ላይ መድረስ እያቃተን ነው፡፡ እኔ የሚመስለኝ አቅርቦቱ ወደ ፍላጎቱ መጠጋቱ አይቀርም፡፡ ግን ዞሮ ዞሮ ኮንስትራክሽን በፍላጎት ውስጥ ነው፡፡ 26 ማይል ርዝመት ብቻ ያላትና ግን በዓለም የሚገራርሙ ሰማይ ጠቀስ የሚገኙባት ኒዮርክ ሲቲ አሁንም ኮንስትራክሽን ላይ ትገኛለች፡፡ አቅርቦትና ፍላጎት ሁልጊዜ እየተጣጣሙ ነው የሚሄዱት፡፡ በእኛም አገር የመንግሥትን አካሄድ ካየነው መዘግየቱ እንጂ በጣም  ብዙ እየተሠራ ነው፡፡ የግሉም ቢሆን የፋይናንስና የውጭ ምንዛሬ ዓይነቱ ችግር ይዞት እንጂ ፍሎጎቱን ለመሙላት እንደሚገባበት እርግጠኛ ነኝ፡፡

ናሽ.ኮን፡- የሪል አስቴት አልሚዎች የቦታ ችግር እንዳለባቸው ይናገራሉ፤ ይህ ሳይፈታ እንዴት መግባት ይችላሉ?

አቶ ሄኖክ፡- ሪል አስቴትን እንደ ኢንቨስትመንት ጥሩ መነሻ ሐሳብ የሚያደርገው የድሮ አሜሪካኖች ካው ቦዮች እንደሚመክሩት መሬት ግዛ የሚሉት ነው፡፡ “ለምን” ተብለው ሲጠየቁም “እግዚአብሔር ከዚህ በኋላ መሬት አይሠራም” ብለው ይመልሳሉ፡፡ ስለዚህ ሁልጊዜም ፍላጎት እየጨመረ አቅርቦት እየጠበበ ነው የሚሄደው ለማለት ነው፡፡ ወደኛ ጉዳይ ስንመለስ አዲስ አበባ ከዚህ በኋላ በተጨማሪ ቦታዎች ወይም መሬቶች የመስፋት ዕድሏን አናውቅም፡፡ ስለዚህ እኔ እንደሚመስለኝ ከጎን ይልቅ ወደ ላይ የመውጣት ነገር ነው፡፡ እየታየ ያለው አካሄድም እንደዚያ ነው፡፡ መቼም ጥሩ ነገር አላሚ /ኦፕትሚስቲክ/ ነኝና ከተማችን ወደፊት ትልቅና ውበታም ትሆናለች፡፡

ናሽ.ኮን፡- አሁን ባለው የኢኮኖሚ ውጣ ውረድ ወደዚህ ለመድረስ ጊዜ አይፈጅም?

አቶ ሄኖክ፡- ብዙ አገራትን እንዳየሁትና ለረዥም ጊዜ በአሜሪካ እንደመኖሬ፣ የአሜሪካንን ሪል እስቴትና ኮንስትራክሽንን ካየኸው አንድ ወደ ላይ አንድ አንድ ወደ ታች ነው የሚሄደው፡፡ ግን ሰላሳና አርባ ዓመት አድርገህ ካየኸው ወደ ላይ ነው የሚወጣው፡፡ የእኛ አገር ግን በተቃራኒው ቀጥ ብሎ ነው የወጣው፡፡ ምናልባት በዚህ ዓመት በአገሪቱ ከተፈጠሩ አለመረጋጋቶችና የፖለቲካ ችግር አንጻር ፈዝዞ ሊሆን ይችላል እንጂ የኢኮኖሚ መውደቅ ምን ማለት እንደሆነ ገና አላየንም፡፡

የአሜሪካን ሪል እስቴት ከባንኮች ጋር በጣም የተቆራኘ ነው፡፡ ስለዚህ ባንኮች እንዲሠሩ ከሚያደደርጓቸው ነገሮች በዋናነት ሪል እስቴት ነው፡፡ ምክንያቱም የሕዝብ ገንዘብ የሚያበድሩት አሴት ይዘው ነው፡፡ ተበዳሪው ባይከፍል ባንኩ የያዘውን አሴት ሸጦ ብሩን የመመለስ ዕድል አለው፡፡ ይህ ሚና በእኛ አገር ሙሉ በሙሉ አልታየም፡፡

ናሽ.ኮን፡- ኢትዮጵያ በ2025 እ.ኤ.አ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለማሰለፍ የተያዘው ዕቅድ ምን ያህል ግቡን ይመታል ይላሉ?

አቶ ሄኖክ፡- ኦፕቲሚስት ነኝ ብያለሁ፡፡ ግን ከባዶ ሜዳ ተነስቼ አይደለም፡፡ እንግዲህ ከዛሬ አሥርና አሥራ አምስት ዓመታት በፊት ከነበርንበት ቦታ አንጻር ስናየው ጥሩ መጥተናል፡፡ ችግር የለም ማለቴ ግን አይደለም፡፡ ነገር ግን ለውጡን በገሃድ ያየነውና ፈጣን ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በዚህ መሠረት ይህ ለውጥ እ.ኤ.አ 2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ያደርሰናል ወይ ብዬ ስመለከት አካሄዱ ጥሩ ስለሆነ እንደርሳለን ባይ ነኝ፡፡ ግን ወደዚህ ለመድረስ መፈታት ያሉባቸው ችግሮች ደግሞ መኖራቸውን ሳንዘነጋ ነው፡፡ ይኸውም የፖለቲካ መረጋጋት እና የፀጥታ ጉዳይ ዐቢይ ነገር ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የተሻለ የግል ኢኮኖሚ ተሳትፎ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እንዳሉ ሆነው ለግሉም ለቀቅ ቢደረግ ጥሩ ነው፡፡ ለምሳሌ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኮሜርሻል ባንክ፣ ሺፒንግ ላይንስ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ ኤልፓ … ዓይነቶቹ ናቸው ዕድገትን እየገፉ በትልቁ ሁኔታ ያመጡት፡፡ ግን እነዚህ ለዘላለም መሸክም አይችሉም፤ መሸከም የሚችለው የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ነው፡፡ ያንን ለመሸከም ደግሞ ዘሩ መዘራት ያለበት አሁን ነው፡፡ እስካሁን ብዙ ሲዘራ ስላላየሁ ማለት ነው፡፡